የድረ-ገጽ አሰራር ለኢትዮጵያውያን የንግድ ባለቤቶች
በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ ያለው የዲጂታል አለም የንግድ ድርጅቶች በኢንተርኔት ላይ የሚኖራቸው የመገኛ ሊንኮችና በተለያዩ ፕላትፎርሞች ላይ ስለ ድርጅታቸው የተለቀቁ ይዘቶች በሽያጫቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር ከጀመረ ቆየትየት ብሏል። ቢሆንም አብዛኞቹ ድርጅቶች ይህን የኢንተርኔት ከፍተኛ የጥቅም ድርሻ እየተጋሩት አይደለም። ለዚህም ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ፦ ስለጉዳዩ ዕውቀት ከማነስ የመጣ የፍላጎት አለመኖር፤ ድርጅታቸውን የሚጠቅም የዲጂታል መገኘት (digital presence) መንገድ ምን አይነት እንደሆነ አለማወቅ፤ የት፣ በማን እገዛና በምን መንገድ እንደሚከወን አለማወቅ፤ የተለያዩ ተያያዥ ግልጋሎቶችን ከአለም አቀፍ አቅራቢዎች ለማግኘት የሚከፈል ክፍያን ማሳለጫ መንገድ አለመኖር ይገኙበታል።
ድረ-ገጽ ለእንድ ድርጅት የዲጂታል መገኛ ማዕከላዊ ስፍራ ሆኖ ያገለግላል። ንብረትነቱም የድርጅቱ ባለቤት ነው። ድርጅቱ በተለያዩ "ፕላትፎርሞች" የከፈታቸው መለያዎቹ (social media accounts) ወይም በሌሎች አካላት ስለድርጅቱ የተለቀቁ ይዘቶችን የተመለከተ ደንበኛ ስለድርጅቱ የተሻለ ገለጻ በሚፈልግበት ወቅት በስርዓት የተደራጀ መረጃ በማቅረብ ያገለግላል። በተጨማሪም ደንበኞች ከድርጅቱ ጋር የዲጂታል መስተጋብር እንዲኖራቸው አካላዊም ሆነ የዲጂታል እድራሻዎችን ማቅረብ፤ መጠይቆችን ማስሞላት፤ የደንበኛውን ፍላጎት መለየት እና እንደ ጉግል፣ ቢንግና ያሁ ያሉ የድር-ፍለጋ ማሽኖች ስለድርጅቱ ይበልጥ እንዲያውቁ በማድረግ በተገቢው የፍለጋ ጥያቄዎች ድርጅቱ ከደንበኛ ጋር እንዲገናኝ ለማድረግ የድረ-ገጾች ሚና ከፍተኛ ነው።
አንድ ድርጅት ድረ-ገጽ እንዲኖረው ካስፈለገ የመጀመሪያው እርምጃ የድር-ጣቢያ ስም (domain name) ማስመዝገብ ነው። ይህን ለማድረግ በኢትዮጵያ ባንኮች በኩል ክፍያ የሚቀበሉና የድር-ጣቢያ ምዝገባ አመቻቺ ድርጅቶች ውስጥ ethiotelecom.et፣ yegara.com እና hahucloud.com የሚጠቀሱ ናቸው።
ሁለተኛው እርምጃ የድረ-ገጹና ኢሜይሎች መስተናገጃ/ ማከማቻ መከራየት ነው። ይህም ድረ-ገጹ ያለመቆራረጥ ለደንበኞች እና የድር-ፍለጋ ማሽኖች እንዲደርስ ያደርገዋል። ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች በተጨማሪነት ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።
ሶስተኛው እርምጃ ድር-አሳሾች (browsers) የድረ-ገጹን ይዘቶች ማንበብ በሚችሉበት ኮድ ማስቀመጥ ነው። ይህም በዋናነት በድረ-ገጽ አልሚዎች (website developers) የሚሰራ ሲሆን፣ እንደ ወርድፕረስ እና ጁምላ ያሉ የጦማር አገልግሎት አቅራቢዎች የኮድ እውቀት በሌላቸው እንዲሰራ ተደርጎ ተዘጋጅቷል። ይህንንም አገልግሎት ያለክፍያ ማግኘት ይቻላል። ለበለጠ መረጃ ይህን ያንብቡ።
መረሳት የሌለበት፡ በድርጅቱ የድር-ጣቢያ ስም የተከፈቱ ኢሜይሎች (ለምሳሌ info@"my-company".com) ደንበኞች ለድርጅቱ የሚኖራቸውን አመኔታ የመጨመር አቅም ያለው በመሆኑ ማሰናዳትና ከድረ-ገጹ ጋር ማያያዝ ጠቃሚ ነው።
በመጨረሻም ድረ-ገጹን ጎብኚዎች በቀላል ፍለጋ ኢንዲያገኙት እንደ ጉግል፣ ቢንግ እና ያሁ ያሉ የፍለጋ ማሽኖች እንዲያነቡት አድርጎ ማስተካከል (SEO) መዘንጋት የሌለበት ስራ ነው። ለበለጠ መረጃ ይህን ያንብቡ።